Background
Daily Devotional
የዕለቱ ጥቅስ

ህዳር

12

በፍጹም ልብህ

የዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል -

ዘዳግም 5-7

በፍጹም ልብህ

''አንተም እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደድ። '' ዘዳግም 6:5


ፍቅር የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው በፍጹም ልባችን እንድንወደው ነው። በመጀመሪያ በመልኩና በአምሳሉ ሲፈጥረን፣ ቀጥሎም እኛን ከሃጢአታችን ለመታደግ በልጁ በኢየሱስ ራሱን ሲሰጠን እርሱ በፍጹም ልቡ እንደሚወደን ግልጽ አድርጎ አሳይቶናል። ታዲያ እንዲህ ባለ ዘላለማዊ ፍቅር የወደደን አምላክ እኛም ለዚህ ፍቅሩ የፍቅርን ምላሽ እንድንሰጥ ይጠይቀናል። 

በእርግጥም በፍጹም ልባችን ልንወደው የሚገባን በፍጹም ልቡ በዘላለማዊ ፍቅሩ የወደደንን አምላካችንን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። 


ይህንን በተመለከተ ኢያሱ ለእስራኤላውያን እንዲህ በማለት ተናግሮአቸው ነበር:- 

“ ስለዚህ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለመውደድ ተጠንቀቁ።” ኢያሱ 23:11

ምንም እንኳን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ያወጣቸው፣ በብዙ የተንከባከባቸውና የረዳቸው፣ ለትልቅም አላማ የጠራቸው አምላካቸው እግዚአብሔር ቢሆንም የእነርሱ ልብ ግን በሌሎች አማልክት ፍቅር ይሸፍት ነበር። ለዚህ ነው “እግዚአብሔርን ለመውደድ” እንዲጠነቀቁ የተነገራቸው። እኛም ልባችንን ሊሰርቁ የሚሞክሩ፣ ከእግዚአብሔር አብልጠን የምንወዳቸው ነገሮች በህይወታች ካሉ ቆም ብለን ራሳችንን እንፈትሽ። 

የሕይወት ምንጭ የሆነውን ልባችንን አጥብቀን መጠበቅ የምንችለው በፍጹም ልባችን እግዚአብሔርን ስንወድ ብቻ ነው። 

አባት ሆይ፣ በፍጹም ልብህ የወደድከንን አንተን እኛም በፍጹም ልባችን እንድንወድህ በጸጋህ እርዳን። አሜን።

መስከረም
ጥቅምት
ህዳር